15 March 2019 Written by 

የኢትዮጵያ ብር እና የውጭ ምንዛሬ ዝውውር

 

መግቢያ

በአንድ አገር ጤናማ የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የኢኮኖሚ እድገቱ የሚመጥን የውጭ ሃገር ገንዘብ ልውውጥ እንዲኖር ማድረግ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት ወደ መካከለኛ ገቢ የሚያደርጉት ግስጋሴ ወሳኝነት አለው፡፡  

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 እንደተሸሻለው በዓንቀፅ 18(6) ፣20 (2) እና 27 (2) መሰረት የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ መመርያ ለማውጣት ስልጣን እንደተሰጠው ስለተደነገገ በተለያዩ ግዚያት መመርያዎች ሲያወጣና ሲያሻሽል ቆይቷል፡፡ በዚሁ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ማነኛውም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እና ሲወጣ ምን ያህል የኢትዮጵያ ገንዘብ ማለትም ብር እንዲሁም በኢትዮጰያ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ምንዛሬ ይዞ መውጣት እና መግባት እንደሚችል በመመርያ ደንግጎ ይገኛል፡፡

በመሆኑም አሁን ስራ ላይ ያለው መስከረም 25/2010 የወጣውን መመርያ ቁጥር FXD /34/49/2017 ሲሆን ይህን መመርያ በዋናነት በስራ ላይ የነበሩትን FXD /34/2007 እንዲሁም መመርያ ቁጥር ወምክሪአዳ/472/09 በመሻር ስራ ላይ የሚገኝ ነው፡፡

የመመርያ ቁጥር FXD /34/49/2017 ይዘቶች

የውጭ አገር ገንዘብ ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ከአዋጅ ቁጥር 591/2000 ዓንቀፅ 2(5) ላይ መረዳት እንደሚቻለው ከኢትዮጵያ ገንዘብ በስተቀር ከኢትዮጵያ ውጭ በማናቸው ሃገር ህጋዊ ገንዘብ የሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረግ ክፍያ ተቀባይነት እንዳለው ብሄራዊ ባንክ ያሳወቀው ማናቸውም ገንዘብ ነው በሚል ትርጉም ተሰጥቶት ይገኛል፡፡በዚህ ትርጉም መሰረት አንድ የውጭ አገር ገንዘብ በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ሟሟላት እንደሚጠበቅበት ይገልፃል፡፡ 1ኛ በሌላ ሃገር ህጋዊ የሆነ ገንዘብ መሆን አለበት፡፡ 2ኛ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ለክፍያ ያሳወቀው መሆን አለበት የሚሉ መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡   

የመመርያው መግብያ (preamble): - ማነኛውም ህግ ሲወጣ የህጉ አስፈላጊነቱ በተመለከተ በመግብያው የሚገለፅ ሲሆን የዚህ መመርያ አስፈላጊነቱ እንደሚከተለው ተገልጧል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡና የሚወጡ መንገደኞች ልይዙት ስለሚገባ የገንዘብ መጠን መወሰን በማስፈለጉ ፣እንዲሁም ሁኔታዎች አና ክልከላዎች የመሳሰሉት ጉዳዮች በሚመለከት ለኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች፣ ነዋሪ ያልሆኑ እና ማነኛውም ሰው የውጭ ምንዛሬ ልይዝበት የሚገባ ሁኔታ መወሰን በማስፈለጉ መመርያውን መውጣቱ በመግብያው ላይ ተገልጿል፡፡የውጭ ምንዛሬ በተመለከተ ነዋሪ የሆነ እና ያልሆነ ሰው የውጭ ምንዛሬ በዚህ መመርያ በተቀመጡት መስፈርቶች መያዝ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን ስለ የተፈጥሮ ሰዎች (physical persons) ብቻ የሚgza ስለመሆኑ ከአጠቃላይ የመመርያው ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡

የመመርያው ስያሜ፡- መመርያ ቁጥር FXD /34/49/2017 የኢትዮጵያ ብር እና የውጭ ምንዛሬ ስለምያዝበት አግባብ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በኢንግሊዘኘው ‘’ Limits on Birr and Foreign currency Holding in the Territory of Ethiopia.’’ በሚል ተገልፆ ይገኛል፡፡

ትርጉም፡- በመመርያው ዓንቀፅ አንድ ላይ ስለ ነዋሪነት በተመለከተ ለዚህ መመርያ አላማ ብቻ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በዚሁ መሰረት

1ኛ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው ማለት የኢትዮጵያ ዜግነት ኖሮት በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ፣ በኢትዮጵያ በነዋሪነት ተመዝግቦ የሚገኝ የሚገኝ የውጭ ሃገር ዜጋ ሆኖ ቋሚ ወይም ግዚያዊ የሆነ መኖርያ በሃገሪቱ ህግ መሰረት የተሰጠው ግለሰብ እንደሆነ በትርጉም ክፍል ተገልፆ ይገኛል፡፡

2ኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆነ ግለሰብ ማለት የኢትዮጵያ ዜግነት ኖሮት ወይም የውጭ ዜጋ ሆኖ የማይኖር እና የመኖር ፍቃድ ያላገኘ መሆኑን ተገልፆ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የጉዞ ሰነድ ማለት እንደ ፓስፖርት እና ሌሎች የጉዞ ሰነዶች ሆኖ በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን ተቀባይነት ያለው ወይም በሌላ ሃገር ተሰጥቶ በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያለው የጉዞ ሰነድ እንደሚያጠቃልል ትርጉም ተሰጥቶት ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ገንዘብ ላይ ወይም ብር ያሉ ገደቦች የተመለከቱ ድንጋጌዎች

በመመርያው ዓንቀፅ 2 ላይ ማነኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እና ከኢትዮጵያ የሚወጡ ኢትዮጵያውን እና የውጭ ዜጎች በተመለከተ በመርህ ደረጃ በእያንዳንዱ ጉዞ ከሃገር ሲወጣ ወይም ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እስከ ብር 1000 (አንድ ሺህ)  ብቻ መያዝ እንዳለበት ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ እቃዎች 90 በመቶ በሚስተናገድበት ጁቡቲ ግን እስከ 4000 (አራት ሺህ) መያዝ እንደሚቻል የተገለፀ ሲሆን በአሁኑ ግዜ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር የገባው የንግድ እና ሌሎች ስምምነቶች ከጁቡቲ ይልቅ ለኢትዮጵያ ቅርብ የሁኑት የምፅዋዕ እና ዓሰብ ወደቦች መጠቀም የሚጀምርበት ሁኔታ በመጨረሻ ምዕራፍ የሚገኝ ስለሆነ ህጉ በዚህ መንገድ ሊሻሻል እንደሚገባ ማየት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ገንዘቦች ያሉ ገደቦች በተመለከተ

በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ገንዘቦች ማለት ምንም እንኳን በመመርያው የተገለፀ ነገር ባይኖርም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በአሰራር እና ደንብ መሰረት የወሰናቸውን የውጭ አገር ገንዘቦች ተብለው ተጠቅሰው የሚገኙ ገንዘቦች መኖራቸውን ግን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ በኢትዮጵያ ተቀባይነት የሌላቸው የውጭ ገንዘቦች ሲገኙ ምን መፍትሄ እንደሚሰጥ የሚታወቕ ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም እዚህ ላይ የሚነሳው ጉዳይ እንደ ውጭ ምንዛሬ የማይያዙ እና ወደ ዶላር እና ብር መቀየር ካልቻሉ ያለው የወንጀል ተጠያቅነት ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም አብዛኛው ባለሙያ እነዚህ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሊመነዘሩ የማይችሉ የውጭ ገንዘቦች በማነኛውም መንገድ ይዞ መገኝት በህግ ሊያስጠይቅ አይገባም የሚል ክርክር ሚዘን የሚደፋ ይመስላል፡፡

መመርያው አብዛኛው ሽፋን በመስጠት የሚያወራበት ጉዳይ የውጭ ምንዛሬ በተመለከተ ሆኖ የውጭ ምንዛሬ ይዞ ስለሚቆይበት የግዜ ገደብ በሚመለከት ከዓንቀፅ 3 እስከ 5 ያለው በንኡስ ዓንቀፆች ተከፋፍሎ በዝርዝር ተገልፆ ይገኛል፡፡ በዚሁ መመርያ ዓንቀፅ 3 ማነኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ የውጭ ምንዛሬ በእጁ ከገባበት ግዜ ጀምሮ ወይም በገቢዎች ዲክሌር ካደረገበት ከ30 ቀን በላይ መያዝ እንደማይችል ደንግጎ ይገኛል፡፡ይህ ማለት በኢትዮጵያ ውሰጥ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ምንም ዓይነት  የውጭ ምንዛሬ ከ 30 ቀናት በላይ የውጭ ምንዛሬ ከተገኘበት ግዜ ይዞ መቆየት እንደማይቻል በግልፅ ኣስቀምጣል፡፡ የውጭ ምንዛሬ መጠኑ ከግምት የሚገባ አይደለም፡፡

የመመርያው ዓንቀፅ አራት በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን 1ኛ ኢትዮጵያ ውሰጥ ነዋሪ የሆነ ሰው ከውጭ ሃገር ሲገባ ከ 1000 ዶላር ወይም በሌላ ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ ከያዘ ዲክሌር ማድረግ እንዳለበት በግልፅ የሚያስገድድ ሲሆን ከ 1000 ዶላር በታች የሚይዝ ግን ዲክሌር ሳያደርግ ይዞ መግባት እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ነገር ግን ይህ ከ 1000 በታች የሆነ የውጭ ምንዛሬ በ30 ቀናት ባንክ ሄዶ የመመንዘር ግዴታ ገብቷል፡፡ ይህን ድክሌር የሚደረግበት ቦታ በተመለከተ ደግሞ በኤርፖርት እና በሌላ ወደ ሃገሪቱ መገቢያ የሆኑ መግብያ ቦታዎች ሁሉ እንደሆነ መመርያው ግልፅ ኣድርጎታል፡፡

2ኛ ኢትዮጵያ ውሰጥ ነዋሪ ያልሆነ ሰው ከውጭ ሃገር ሲገባ ከ 3000 ዶላር ወይም በሌላ ተመጣጣኝ ውጭ ምንዛሬ ከያዘ ዲክሌር ማድረግ እንዳለበት በግልፅ የሚያስገድድ ሲሆን ከ 3000 ዶላር በታች የሚይዝ ግን ዲክሌር ሳያደርግ ይዞ መግባት እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ይህን ድክሌር የሚደረግበት ቦታ በተመለከተ ደግሞ በተመሳሳይ በኤርፖርት እና በሌላ ወደ ሃገሪቱ  መግብያ ቦታዎች ሁሉ እንደሆነ መመርያው ግልፅ ኣድርጎታል፡፡ እዚህ ላይ የዓንቀፅ 3 እና 4 ያለው ልዩነት ግልፅ መሆን ያለበት ሲሆን በዓንቀፅ 3 መሰረት ማነኛውም ሰው የውጭ ምንዛሬ ካገኘበት ግዜ ጀምሮ ቁጥሩ ከግምት ሳይገባ ከ 30 ቀናት ውስጥ ባንክ ሄዶ መመንዘር እንዳለበት ሲገልፅ ዓንቀፅ 4 ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና ያልሆኑ ግለሰቦች በተለያያ አጋጣሚ ወደ ውጭ በሚኖራቸው ጉዞ ሲመለሱ ወይም በተለያየ አጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ዲክሌር ሳያደርጉ ይዘው መግባት እንደሚችሉ ለመጠቆም ሲሆን በዚህ መንገድ የገባው የውጭ ምንዛሬ ግን በ 30 ቀናት ባንክ ተሂዶ መመንዘር እንዳለበት የሚያስገድድ ዓንቀፅ ስለሆነ ሁለቱ የሚደጋገፉ እንጂ የሚቃረኑ አይደሉም፡፡

እዚህ ላይ ያለው ልዩነት ግልፅ ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ በ30 ቀናት ውስጥ ዲክሌር ማድረግ ሲጠበቅበት ነዋሪ ያልሆነ ግለሰብ ግን የቪዛው ቆይታ የሚወስነው መሆኑን ማለትም ቪዛው ፀንቶ እስከሚቆይበት ግዜ ይዞ መቆየት ይችላል፡፡ ይህ ማለት ነዋሪ ያልሆነ ሰው ነዋሪ ከሆነ ሰው የበለጠ መብት ተሰጥቶት ይገኛል፡፡

ወደ ውጭ በሚደረግ ጉዞ ሲለሚፈቀድ የውጭ ምንዛሬ

ይህ በዓንቀፅ 4.3 በግልፅ የጠቀመጠ ሲሆን በ 3 ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

1ኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ  ስለሆኑ ሰዎች የተመለከተ ሲሆን ማነኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ የባንክ ፍቃድ ወይም ዲክሌር ያደረገበት ሰነድ እስካቀረበ ድረስ ይዞ መውጣት ይችላል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ይዞ የሚሄድ ሰው የውጭ ምንዛሬው ካገኘበት ግዜ 30 ቀን ያላለፈው ከሆነም ይዞ መሄድ ይችላል (ዓንቀፅ 4.3.1) ፡፡ የዚህ ዓንቀፅ መልእክት ወይም ድምዳሜ ሲታይ ምንም ዓይነት ፍቃድ ሳይኖር እና ፍዳዱም 30 ቀን ያለፈው ከሆነ ይዞ መሄድ እንደማይችል በግልፅ ከላይ በተቀመጠው ዓንቀፅ ተመላክተዋል፡፡

2ኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆነ ግለሰብ ከሆነ ግን ከ 3000 የአሜሪካን ዶላር በላይ ይዞ የሚወጣ ሰው የባንክ ፍቃድ ወይም በጉምሩክ ዲክሌር ያደረገበት ሰነድ ማቅረብ አለበት፡፡ ከ3000 ዶላር በታች ከሆነ ግን ምንም ፍቃድ ሳይዝ ይዞ መውጣት እንደሚችል የመመርያው ዓንቀፅ 4.3.2 ይፈቅዳል፡፡

3ኛው በዓንቀፅ 4.3.3 በልዩ ሁኔታ ለኤምባሲ ሰራተኞች፣ግዚያዊ የውጭ ሃገር ሰራተኞች፣እንደዚሁም የወርክሾፕ ተሳታፊዎች እና ሰልጣኞች በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆነ ግለሰብ ያለው መብት ተስጥቶዋቸው ከ3000 የአሜሪካን ዶላር በላይ ይዞ የሚወጣ ሰው የባንክ ፍቃድ ወይም በጉምሩክ ዲክሌር ያደረገበት ሰነድ ማቅረብ አለበት፡፡ ከ3000 ዶላር በታች ከሆነ ግን ምንም ፍቃድ ሳይኖር ይዞ መውጣት ይቻላል፡፡

ስለ ቅጣት

አንድ ህግ ተፈፃሚ የሚሆነው ለክልከላው ተገቢና ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ሲኖር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ መመርያ መሰረት በብሄራዊ ባንክ ኣዋጅ ቁጥር 591/00 ዓንቀፅ 26 መሰረት እንደሚቀጣ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በህጉ ዙርያ የሚነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች እና ክርክሮች

ከመስከረም 25/2010 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው መመርያ ቁጥር FXD /34/49/2017 ብዙ ጥያቄዎች ይነሳበታል፡፡ በህጉ ራሱ እና በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ግንዘቤ በሚል የሚነሱ ክርክሮች እንደሚከተለው አንድ በአንድ ለማየት ጥረት ይደረጋል፡፡

መመርያ የወንጀል ተጠያቂነት ማስከተሉ በተመለከተ

1ኛ ይህ ብሄራዊ ባንክ ያወጠው መመርያ የወንጀል ሃላፊነት ማስከተል ስለመቻሉ የሚለው በቅድምያ የሚነሳ ክርክር ነው፡፡ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ በህግ ደረጃ በልማድ እንዲሁም በዳበረ ስርዓት ውስጥ በአዋጅ እና በኮድ መልክ ተቀርፀው ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ የህግ ባለሙያዎች በመመርያ ደረጃ የወንጀል ተጠያቂነት ሊያስከትል አይገባም የሚል ጠንካራ መከራከርያ ሲያቀርቡ ይታያሉ፡፡ የመመርያዎች ዓላማ ሲታይ በአዋጅ የተደነገጉት ይበልጥ ዝርዝር በማድረግ ለአፈፃፀም ምቹ ማድረግ መሆኑ ከአስተዳደር ህግ መርህና ተግባር መረዳት ይቻላል፡፡ስለዚህ መመርያውን የሚያወጣው አካል ወንጀል ብሎ አንድን ጉዳይ ለመደንገግ ስልጣን ስላልተሰጠው ባልተሰጠው ስልጣን የወንጀል ድንጋጌ መፍጠር እና እንዲፈፀም ማድረግ የራሱ ችግር ያለበት ነው በሚል ክርክር የሚያቀርቡ ባለሙያዎች አሉ፡፡

ከዚህ በተቀራኒው ደግሞ የመመርያው ዓላማ የወንጀል ተግባር ለመደንገግ ሳይሆን የተቀመጠው ገደብ ከመግለፅ ውጭ ተጠያቂነቱ የሚመጣው በሌላ ህግ ነው የሚል ጠንካራ ክርክር ይቀርባል፡፡ መመርያው ብሄራዊ ባንክ በአዋጅ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ ገደብ ማውጣት እንደሚችል ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የዚህ መመርያ ዋና ዓላማ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ ህጋዊ የሆነ ገደብ ማበጀት ነው፡፡ ይህ መመርያ ብቻውን የሚቆም ሳይሆን ከጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ዓንቀፅ 168 ጋር አብሮ መታየት ያለበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በጉምሩክ አዋጅ መሰረት በወንጀል የሚስጠይቅ ተግባር የጉምሩክ ስነስርዓት ያልተፈፀመበት፣ ገደብ የተደረገበትና የተከለከለ ሲሆን እንደሆነ ህጉ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ ስለዚህ ይህ ብሄራዊ ባንክ ያወጣውን መመርያ ገደብን መሰረት አድርጎ የወጣ ስለመሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ክስ ለመመስረት መመርያውና የጉሙሩክ አዋጁን በጣምራ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በተግባር እየተሰራበት ያለውም ይህ አሰራር ነው፡፡

 የትራንዚት መንገደኞች በተመለከተ ያለው የህግ ተጠያቂነት

በዚህ ረገድ ህጉ የሚለው ነገር አለመኖሩ የራሱ የሆነ ክፍተት ፈጥራል፡፡ ቀደም ሲል የትራንዚት መንገደኞች በተመለከተ ማነኛውም ከትራንዚት ክልል እስካልወጣ ድረስ የውጭ ምንዛሬ ይሁን ሌላ ነገር ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚችል የፈቀደበት አግባብ ነበር፡፡መንገዶኞች ከትራንዚት ክልሉ በመውጣት ወደ ከተማ የውጭ ምንዛሬ ይዘው የሚገቡበት ሁኔታ በልዩ ሁኔታ እየታየ ሊወሰን የሚገባው ነው፡፡ ከትራዚት መንገደች ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ የትራንዚት መንገደኞች በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሌሎች ሃገራት የሚመላለሱ ግለሶበች በተለያያ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ሲረግጡ እና በጉምሩክ ህጉ መሰረት ከጉምሩክ ክልል ሲወጡ በኢትዮጵያ የመኖርያ ስፍራ እንደሌላቸው  ተቆጥረው ሊታዩ የሚገባ ይመስላል፡፡ በዋናነት ግን የትራንዚት መንገዶች በተመለከተ የሚከተሉት አካራካሪ ነጥቦች ማንሳት የሚቻል ይሆናል፡፡

1ኛ የትራንዚት መንገደኛ የማረፍያው የመጨረሻ ጉዞው ለመድረስ እንጂ በሌላ ሃገር የሚቆሙ እና የሚያርፉ ስለመሆናቸው የሚያውቁት ነገር ስለሌለ እና የሚያጓጉዛቸው አየር መንገድ መንገድ ላይ በሚያጋጥሙት ችግሮች እንዲያርፉ ሲደረግ ያለው ወንጀል የማድረግ ሃሳብ ሊጠና የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው በወንጀል ሊቀጣ የሚገባው የወንጀል ሃሳብ ሲኖረው እና አልያም ቸልተኝነት በሚኖርበት ግዜ ብቻ ስለመሆኑ ከወንጀል ህጋችን የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የትራንዚት መንገደኞች የሚይዙት ማነኛውም እቃ ይሁን ገንዘብ መሄድ ወደሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ እንጂ በመሃል እንዲህ ዓይነት ችግር ይገጥመናል በሚል የሚያስቡት አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የሚያዙ ግለሰቦች የወንጀል ሃሳብ የሌላቸው ስለሆነ በወንጀል እንዲጠየቁ ማድረጉ ተገቢነት የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌ/ጠ/ዓ/ህግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሮ ክስ ያቋረጠላቸው በርካታ የውጭ ዜግነት ያላቸው የትራንዚት መንገደኞች የቅርብ ግዜ ውሳኔ ነው፡፡

ሌላው ከትራንዚት መንገደኞች ጋር ተያይዞ የሚታየው ጉዳይ የትራንዚት መንገደኞች ስለያዙት እቃዎች የራሳቸው ስለመሆኑ ደረሰኝ ወይም ሌላ ማነኛውም ማስረጃ ሲያቀርቡ የሚይዙት ማስረጃ ከሚመለከተው አካል ስለ ትክክለኛነቱ ባይረጋገጥም ደረሰኝ ካቀረቡ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚገባ ነው፡፡

3ኛ ሌላው የህጉ ተፈፃሚነት በተመለከተ ወደ ሃገር ከሚገቡ እና ከሚወጡ ጋር ብቻ የማገናኘት ሁኔታው እንዴት ይታያል የሚለውም መታየት ያለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ሃገር ከመግባትና ከመውጣት ጋር ያልተያያዙ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር በመሃል አገር እና ከተማ ቢገኝ እንዴት ይታያል የሚለው ጉዳይ መታየት አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚኖረው ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ከወንጀል ህጉ ዓንቀፅ 346 እና ከጉምሩክ አዋጅ እንዲሁም ከመመርያው ጋር አገናኝቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡

ሌላ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዞ የሚነሳው ጉዳይ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው የንቃተ ህግ ግንዛቤ በተመለከተ ነው፡፡ ህጉ ተፈፃሚ የሚሆነው በአጠቃላይ በዓለም ዓቀፍ ተጋዦች እና የሌሎች ሃገራት ዜጎች እንደመሆኑ መጠን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በመግብያ እና መውጫ ቦታዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በተለያየ ዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች መሰጠት ያለበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በጋራ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

4ኛ መንግስት ያጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማግኘት በከፍተኛ መጠን በከተማው ህጋዊ በሚመስል መልኩ ሰዎች የውጭ ምንዛሬ ስራ ሲሰሩ መታየቱ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ያስገደደው በመሆኑ በቅርብ ግዚያት የዘመቻ የሚመስሉ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር የቅርብ ግዜ ሁነት ነው፡፡ ነገር ግን የወንጀል ህግ 346 ሲገባ እና ሲወጣ ያልተያዘ በመሃል ከተማ ውስጥ የተያዘ የውጭ ምንዛሬ የወንጀል ተጠያቂነት በምን መልኩ ወይም በየትኛው ህጉ ማስጠየቅ እንዳለበት ግልፅ የሆነ ህግ ስለሌለ  በሚገባ ማየትና መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር ህጉ ከመመርያው ጋር አብሮ ማየት የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ማለትም ገንዘብ እንደ እቃ ስለሚቆጠር ከጉምሩክ ህግ ጋር አብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት አንደ ማነኛውም የጉምሩክ ህጉ እቃ የሚለው ገንዘብም ስለሚያካትት በዚህ አግባብ መተርጎም ያለበት ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በገቢና ወጪ ላይ ያልተያዘ የኮንትሮባንድ እቃ ነው ተብሎ እንደሚያዘው ሁሉ ገንዘብም ሲገባ እና ሲወጣ ካልተያዘ ከጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ዓንቀፅ 168(2) ጋር አብሮ ታይቶ የወንጀል ተጠያቂነቱ በዚህ አግባብ ቢታይ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

በአጠቃላይ ከትራንዚት መንገደኞች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ከጉዳዮቹ አንፃር (case by case) ጋር እየታየ መወሰን ያለበት ነው፡፡ ማለትም የባለጉዳዮች ወደ ሃገር የመግባት ሃሳብ እና ሌሎች ተዛማጅ ሁኔታዎች እየታየ መወሰን ያለበት ነው፡፡

በሃገር ውስጥ እንዲሁም በገቢና ወጪ ላይ ያለው የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ ያለው የወንጀል ተጠያቅነት

የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ በሃገር ውስጥ እንዲሁም በገቢና ወጪ ላይ ሊሆን እንደሚችል የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም የውጭ ሃገር ገንዘብ ዝውውር በተመለከተ በሃገር ውስጥ እንዲሁም በገቢና ወጪ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚታወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገንዘብ በተመለከተ ከሆነ በገቢና ወጪ ላይ ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብር በሃገር ውስጥ መያዝ በወንጀል ስለማያስጠይቅ በወጪና ገቢ ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በዋናነት በዚህ ጉዳይ በወጪና ገቢ የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ ሊታይ የሚገባው በጉምሩክ ህግ መሰረት ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ሌላው አብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ በሃገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ቢገኝ እንዴት መሆን አለበት የሚለው ጉዳይ ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚቀርቡ ጉዳዮች በወንጀል ህግ ዓንቀፅ 346 ማለትም ምንም ፍቃድ ሳይኖር የውጭ ምንዛሬ በመሃል አገር ወይም ከተማ ተይዞ ሲገኝ በህጉ መሰረት በወንጀል ህጉና የባንክ ስራ አዋጅ መሰረት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከገቢና ወጪ ጋር ተያይዞ የሚያዝ ገንዘብ ማለትም ብርም ይሁን የውጭ ገንዘብ በዚህ መመርያ እና በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 መታየት ያለበት ሲሆን እንዲሁም በአገር ውስጥ ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖር የሚያዘው የውጭ አገር ገንዘብ በወንጀል ህግና በባንክ ስራ አዋጅ መታየት ያለበት ነው፡፡

የባለድርሻ አካላት ሚና

የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመቀነስ እና ለመግታት የተለያዩ የመንግስት አካላት ሚና ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በዋናነት ግን በዚህ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የፀጥታ ኣካለት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሚና

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 እንደተሸሻለው በዓንቀፅ 18(6) ፣20 (2) እና 27 (2) መሰረት የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ መመርያ ለማውጣት ስልጣን ስለተሰጠው በዚሁ አግባብ ከአገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ እድገት እና የውጭ ምንዛሬ መሰረት በማድረግ ለቁጥጥሩ ተገቢ እና አጋዥ የሆነ ህግ የማውጣት ግዴታ አለበት፡፡ በዚሁ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በማድረግ የተለያዩ መመርያዎች ሲያወጣ እና ሲያሻሽል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የሚወጣው ህግ ተፈፃሚ የሚሆነው የሌሎች የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና እገዛ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ ባንክ ህጉን ሲያወጣ የህጉ ተፈፃሚነት እንዲሁም በተግባር የሚያጋጥሙት የአፈፃፀም ችግሮች የመገምገም እና የመሰብሰብ ግዴታ አለበት፡፡  

የገቢዎች ሚኒስቴር፣የጉምሩክ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሚና

የገቢዎች ሚኒስቴር አንደ አዲስ በአሰፈፃሚው አካል በሚንስቴር መስርያ ቤት ደረጃ የተዋቀረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽን ደግሞ ለገቢዎች ሚኒስቴር ተጠሪ ሆነ በመደራጀት ያለ ተቋም ሲሆን ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በሚል የአገር ውስጥ ገቢና የጉምሩክ ጉዳዮችን በጣምራ ሲከታተል የነበረ ተቋም ነው፡፡በመሆኑም የጉምሩክ ኮሚሽን በዋናነት በገቢ፣ ወጪ እና ሌሎች ከጉምሩክ አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ጋር ያሉ ጉዳዮች የሚከታተል ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ አብዛኛው ግዜ ከገቢና ወጪ መንገዶኞች ጋር በብዛት የሚያያዝ በመሆኑ ተገቢውን የቁጥጥር ስራዎች የሚሰራበት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በቅንጅት የሚሰራ ስራ ነው፡፡ ስለዚህ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በህገወጥ በህገወጥ መንገድ በሚገቡ እና በሚወጡ የኢትዮጵያ ገንዘብና የውጭ አገር ገንዘቦች የመቆጣጠር ከፍተኛው ሚና አለው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ የጉምሩክ ህግ ከእቃዎች ጋር ተያይዞ የሚፈፀም ህግ በመሆኑ እና በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859 ዓንቀፅ 3 በግልፅ እንደተመላከተው የኢትዮጵያ የጉምሩክ ህጎች በገቢና ወጪ እቃዎች፣ ትራንዚት በሚያደርጉ እቃዎች እነዲሁም በጉምሩክ ቁጥጥር ስለሚውሉ እቃዎች የሚመለከት ነው፡፡ በጉምሩክ አዋጅ 859 ዓንቀፅ 2(1) መሰረት እቃ ገንዘብንም እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡ መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ በቦሌ አውሮፕላን ሲገቡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባባር በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች ወደ ኢትዮጵያ ይዞ መግባት ስለሚቻለው የገንዘብ መጠን መግለፅ፣ ማስተማር እና ይህንኑ ህግ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማስተላለፍ አለበት፡፡

የፌ/ጠ/ዓ/ህግ እና የፌዴራል ፖሊስ ሚና

የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ህግ በሃገሪቱ የሚወጡ የፌዴራል ህጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ክትትል የማድረግ ሃላፊነት እንደተሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ህግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ግልፅ በማድረግ አስቀምጦታል፡፡ ስለዚህ በዚህ አዋጅ መሰረት በዋናነት የወንጀል ጉዳይ በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ህግ የወንጀል ጉዳይ በተመለከተ ምርመራ የመምራት እና የመክሰስ ሰልጣን የተሰጠው ሲሆን በዚህ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ የህግ ማእቀፉን የማሻሻል እና ተግባራዊ የማድረግ እንዲሁም ህጉ ተፈፃሚ ሲሆን የሚያጋጥሙ ችግሮች እየለየ መፍትሄ ማበጀት አለበት፡፡ የፌደራል ፖሊስ ደግሞ በፌዴራል ህጎች ላይ ምርመራ የማድረግ ስልጣን አለው፡፡ በዚሁ መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ የህግን ዓላማ በሚያሳካ እና የማስረጃ አሰባበሰብ ሁኔታም ተከሳሽችን ጥፋተኛ በሚያስደርግ መልኩ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግና የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች ከላይ የገለፅናቸው ባለድርሻ አከላት ጋር አብረው በመስራት የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለማስቆም የድርሻቸው ሊወጡ ይገባል፡፡  

 

ማጠቃለያ

የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ስለ ኮንትሮባንድ ወንጀል በተመለከተ በዓንቀፅ 168 ስር የጉምሩክ ስነ ስርዓት ሳይፈፀምባቸው፣ ገደብ የተደረገባቸው እንዲሁም የተከለከሉ እቃዎች ሲገቡና ሲወጡ ከተያዙ እንዲሁም ደግሞ በመግብያና መውጫ ሳይያዙ ሲቀሩ የሚታይበትና ተፈፃሚ የሚሆንበት አግባብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 እንደተሸሻለው በዓንቀፅ 18(6) ፣20 (2) እና 27 (2) መሰረት የገንዘብ ዝውውር በተመለከተ መመርያ ለማውጣት በተሰጠው ስልጣን መሰረት ማነኛውም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እና ሲወጣ ምን ያህል የኢትዮጵያ ገንዘብ ማለትም ብር እንዲሁም በኢትዮጰያ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ምንዛሬ ይዞ መውጣት እና መግባት እንደሚችል በመመርያ ደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚሁም መሰረት አብዛኛው ግዜ በመግቢያና መውጫ ላይ የሚደረጉ የክልከላ መተላለፍ ከአዋጅ ቁጥር 859/2006 በዓንቀፅ 168 ጋር እየታየ እየተሰራበት የሚገኝ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና ነዋሪ ያልሆኑ ግለሰቦች ስለ ህጉ ያላቸው ግንዛቤ በተለያየ መንገድ እንዲያድግ መደረግ ያለበት ሲሆን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ተጠያቂ እንዲደረጉ ማድረግ የራሱ የሆነ ተፅእኖ በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አይደለም የህግ እውቀት የሌላቸው ሰዎች የህግ እውቀት ያለን እንኳን ከዚህ ዳይሬክቶሬት ውጭ ያለ ባለሙያ የሚያውቀው አይደለም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በሃገሪቱ የመውጫና መግብያ ቦታዎች ማለትም በቦሌ ዓለም ዓቀፍ ኤርፖርት እና በሃገሪቱ ድንበር የሚገኙ ኬላዎች በጉምሩክ ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚገባቸው የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች ማሳወቅ ያለበት የግድ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

Last modified on Friday, 15 March 2019 20:48
mebrihi

The blogger is a Federal Public Prosecutor at The Federal Attorney General Economic Crimes Directorate and a part time Law Instructor at Bahirdar University continuing and Distance Education lecturing Law of Evidence, Fiscal Federalism, Environmental Law, Law of Sales and security devices, Gender and The Law.